የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ደሞዝ አልተከፈላቸውም – DW – 16 ሰኔ 2015
  1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ደሞዝ አልተከፈላቸውም

ዓርብ፣ ሰኔ 16 2015

የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ባለፉት 2 ወራት ደመወዝ ስላልተከፈላቸው ለችግር መጋለጣቸውን አስተወቁ ። ፋብሪካው በጸጥታ ችግር ምክንያት ከግንቦት 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ማቆሙን ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፋብሪካው ሠራተኞች አብራርተዋል ።

https://p.dw.com/p/4SzxD
Fincha sugar factory
ምስል Negassa Dessalegn/DW

የ2 ወራት ደመወዝ አልተከፈለንም ብለዋል

የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ባለፉት 2 ወራት ደመወዝ ስላልተከፈላቸው ለችግር መጋለጣቸውን አስተወቁ ። ፋብሪካው በጸጥታ ችግር ምክንያት ከግንቦት 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ማቆሙን ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፋብሪካው ሠራተኞች አብራርተዋል ። ግንቦት 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም በተከሰተው ጥቃትም በርካታ ንብረቶች መዘረፋቸውንና መኪናም መቃጠሉን አክለዋል ። «የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ» የተሰኘው የሠራተኞች ማኅበር በበኩሉ ክፍያው ያልተፈጸመው በአካባቢው ባንክ አገልግሎት ላይ ባለመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል ። 

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሱሉላ ፍንጫ በተባለ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የፍንጫ ስኳር ፋብሪካ በሚሊዮን የሚቆጠር ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም አለው፡፡ ከፋብሪካው የተገኘው መረጃ እንደያመለክተው በ2012 ዓ.ም 1.1 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ለተጠቃሚው አቅርቧል፡፡ ግንቦት 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ደግሞ በአካባቢው በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሥራ ማቆሙ ተነግሯል፡፡ በፍብሪካው በቋሚነት የሚሠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የወር ደመወዝ እንዳገኙ ያነጋርናቸው የፋብሪካው ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የፋብሪካው ሠራተኛ ለሁለት ወራት ያህል የወር ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ተናግረዋል፡፡   

በግንቦት 12 በስፍራው በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና ሸማቂዎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የተነገሩት ሌላው የፋብሪካው ሠራተኛ በዕለቱ ኮምፒውተሮችና የፋብሪካው ተሽከርካሪ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡ በጸጥታ ኃይሎች እና ሸማቂዎች ጉዳት መድረሱን ገልጸው ከጥቃቱ ወዲህ ፋብሪካው ሥራ አለመጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ሠራተኞችም ወርኃዊ ክፍያ ባለማግኘታቸው ለችግር መጋለጣቸውን አክለዋል፡፡

የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፦ ፎቶ ከማኅደር
የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Negassa Dessalegn/DW

በፍንጫ የጸጥታ ችግር በተከሰተበት ግንቦት 12 አስቀድሞ ከፍብሪካው አቅራቢያ የተኩስ ድምፅ እንደነበር ስሜ አይጠቀስ ያሉ ሌላው የፍንጫ ስኳር ፍብሪካ ሠራተኛ ተናግረዋል፡፡ በጸጥታ ችግር ሳቢያ በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት እና የመድኃኒት እጥረት በመኖሩ ብዘዎች በወቅቱ መታከም እንዳልቻሉም አብራርተዋል ። 
"መኪና እና መዱኃኒት የለም ፡፡ በህክምና እጦት ሕይወቱ ያለፈ ሰው አለ፡፡ አለብነትም ምትኬ አብድሳ የምትባል አንድ የፍብሪካው ሠራተኛ ነፍሰጡር ነበረች በኅመም ምክንያት ሐኪም ቤት ሳትደርስ ሕይወቷ አልፈዋል፡፡ ሠራተኞች ለወራት ክፍያ አላገኙም፡፡ ከተከሰተው ፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ገንዘብ የሚመጣበት መንገድ የለም፡፡ አንድ አንድ ኮምፒውተሮችም ከቦታቸው ስለተነሱ ፋብሪካው ደመወዝ መክፈል አይችልም» የሚል ነው የመለሱት፡፡   

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱትሪ ግሩፕ የሠራተኛ ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ጋዲሳ ደሳለኝ የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቋሙ በሥራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው የሠራተኞችን ቅሬታ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በሆሮ ጉደሩ ወለጋ የሱሉላ ፍንጫ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደረጄ ወርቁ ከወር በፊት በደረሰው ጥቃት ጉዳት መድረሱን ያረጋገጡ ሲሆን በሰው ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን ግን መግለጽ አልፈለጉም፡፡

" የጸጥታ ችግሩ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ ባንክ ዝግ ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ የጸጥታ ሀይሎች ባደረጉት ጥረት ዝርፍያ በሚያካሄድው ታጣቆ ጫካ ውስጥ በሚንቀሳስ ሐይል ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ የተዘረፉ ንብረቶች እና ዝርፍያ የፈጸሙ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ለአንድ እና ሁለት ቀን ነው መንገድ የተዘጋው፡፡ በፍብሪካው ለሸንኮሩ ምርት የሚሆንን ማዳበሪያ ተዘርፏል፡፡ አብኛውን የጸጥታ ኃይል መልሷል፡፡ የፋብሪካው መኪናም በዚህ የጥፋት ኃይል ተወሰዶ የተቃጠለም አለ፡፡ አሁን አካባቢው፣ መንገዱም ሰላም ነው ወደ ሻምቡ መሄድ ቻላል" ብለዋል፡፡

የፍንጫ ስኳር ፋብሪካ በኢትዮጵያ ካሉት የስኳር ፋብርካዎች በተሻለ መልኩ በ2012 ዓ.ም ለንጽህና መጠበቂያ ግብዓት የሚሆን ኤታኖል አምርቷል፡፡ በወቅቱ 11 ሚሊዩን ሊትር ኤታኖል ማምረቱን ከፍብሪካው የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡ ሱሉላ ፍንጫ ወረዳ ከሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ ሻምቡ በ74 ኪ.ሜ ርቅት ላይ ይገኛል፡፡ 

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ