የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ያማረረው የትራንስፖርት አገልግሎት – DW – 28 ኅዳር 2016
  1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ያማረረው የትራንስፖርት አገልግሎት

ዓርብ፣ ኅዳር 28 2016

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ የሚነገርለት የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር እልባት ያላገኘ እና እያደገ የመጣውን የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥርን ያላገናዘበ ነው በሚል ይተቻል። የከተማዋ ነዋሪዎች በመንገዶች መጨናነቅ መንገድ ላይ ከሚያቃጥሉት ጊዜ በተጨማሪ ትራንስፖርት ለመጠበቅም በቀን ውስጥ ሰዓታትን እንደሚያሳልፉ በምሬት ይገልጻሉ፡፡

https://p.dw.com/p/4ZwOa
አዲስ አበባ ከተማ በከፊል
አዲስ አበባ ከተማ በከፊልምስል Seyoum Getu/DW

የመዲናዋን ነዋሪዎች ያማረረው የትራንፖርት ችግር

በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጨመረ መምጣቱ የሚነገርለት የትራንስፖርት አገልግሎት  ችግር  እልባት ያላገኘ እና  እያደገ የመጣውን የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥርን ያላገናዘበ ነው በሚል ይተቻል፡፡ በመዲናዋ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ነዋሪዎቿ በመንገዶች መጨናነቅ የተነሳ መንገድ ላይ ከሚያቃጥሉት ጊዜ በተጨማሪ ትራንስፖርት ለመጠበቅም በቀን ውስጥ ሰዓታትን እንደሚያሳልፉ በምሬት ይገልጻሉ፡፡የትራንስፖርት እጥረቱና የአገልጋዮች ስነምግባርም በተሳፋሪዎቹ እንደጉድለት ከሚነሱ ናቸው፡፡
ዳምጤ ማሞ ይባላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የኮተቤ አከባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ይህ መኖሪያ አከባቢያቸው በመዲናዋ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ከሚስተዋልባቸው ተጠቃሽ ነው የሚሉት አቶ ዳምጤ የስራ ቦታቸው ከመኖሪያቸው በመራቁ የትራንስፖርቱን ብርቱ ሰልፍ መጋፈጥ ግድ ብሎአቸዋል፡፡ “ትራንስፖርት በጣም ችግር ነው፡፡ ለአንድ ጉዞ አውቶብስ ለመጠበቅ አንዳንዴ እስከ አንድ ሰዓት እንቆማለን፡፡ ተኩል ሰዓትማ መቆም የተለመደ ነው፡፡ በተለይ በስራ መግቢያና መውጫ ችግሩ ከባድ ነው” ይላሉ፡፡ ተሳፋሪው ችግሩ ሲብስ እንጂ ሲቀልም እንዳላስተዋሉ ነግረውናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግር
የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግርምስል Seyoum Getu/DW

በላይነህ መኮንን ደግሞ ከሽሮ ሜዳ ወደ ለገሃር እና ከዚያ መልስ መመላለሳቸው የሰርክ ተግባራቸው ነው፡፡ ላለፉት 16 ዓመታት በዚሁ የትራንስፖርት ብርቱ ፈተና ተመላልሻለሁ የሚሉት አስተያየት ሰጪው አሁን ግን ችግሩ ሰፍቷል ሲሉም ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ “ችግሩ በጣም ከባድ ነው፡፡ የማይቻል ወደ መሆን ደረጃ እየተሸጋገረ ነው፡፡ ግን ከዚህ የምንረዳው ህዝቡ ወደ አዲስ አበባ እየገባ ነው የሚወጣ ግን የለም፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች ግን ያው ናቸው በየጊዜው አይጨመሩም” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከኮተቤ ወደ ስታዲየም አከባቢ ዘወትር እየተመላለሰች ስራ በመስራት ህይወቷን የምትመራው የባንክ ሰራተኛዋ ወጣት ውቢት አዲሱም ተመሳሳ አስተያየቷን አጋርታናለች፡፡ “አነሰ ሲባል ትራንስፖርት ለማግኘት 30 ደቂቃ እንጠብቃለን” የምትለው ወጣት ውቢት ችግሩ የታክሲ አገልግሎት ሰጪም ሆነ ትልልቅ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪውም ጋ ነው ትላለች፡፡
ከቃሊቲ ወደ ለገሃር እየተመላለሰ በየቀኑ ህይወቱን የሚገፋው ወጣት ዮሃንስ ሹምዬም በአስተያየቱ የችግሩ ስፋት ሲያስረዳ፡ “ጠዋት ስራ ለመግባት 11 አሊም 12 ሰዓት ከቤት ተነስተን ከቤት መውጣት አለብን፡፡ 12፡30 እንኳ ብንወጣ በትራንስፖርት ጥበቃ ስራ ይረፍድብናል” ሲል ይገልጻል፡፡
ከአስኮ ወደ መስቀል አደባባይ በየቀኑ በመመላለስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ትምህርቷን የምትከታተለው ያምላክ ፍቃዱም የትራንስፖርት ችግሩን አስከፊ ስትል ትገልጻለች፡፡ “ያው ተማሪ እንደመሆኔ ባስ ነው የምጠቀመው፡፡ የትራንስፖረት ችግር ሰፊ ነው፡፡ ወደ ትምህርት ለመሄድ በትንሹ ከ30-40 ደቂቃ ቆሜ እጠብቃለሁ” ስትል ችግሩን አብራርታለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ያማረረው የትራንስፖርት ችግር
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ያማረረው የትራንስፖርት ችግር ምስል Seyoum Getu/DW

መተዳደሪያው በሆነው የብሬት ብየዳ ላለፉት 10ርት ዓመታት መስራታቸውን የሚገልጡት አቶ ጉተማ ቱጁባም ጠዋት ማተውን ከመኖሪያቸው ገላን ኮንዶሚኒየም ለገሃር ይመላለሳሉ፡፡ አንዲት ባስ ብቻ ጠዋት ማታውን በዚህ ትመላለሳለች የሚሉት አቶ ጉተማ ያቺኑን ለመጠበቅ ከአንድ ሰዓት በላይ የሚቆሙበት ጊዜ መኖሩንም አስረድተዋል፡፡ “አንድ ሰዓት እንቆማለን ለጥበቃው ብቻ፡፡ ችግሩ የሚገለጽ አይደለም በጣም ከባድ ነው” ብለዋል፡፡ተሳፋሪዎቹ የችግሩ ስፋት በእለት እለት ስራቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉንና በብርቱ እንደፈተናቸው ያስረዳሉ፡፡ መፍትሄ ያሉትን ሲያስረዱም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎችን መጨመር እና በኃላፊነት አገልግሎቱን ማቀላጠፍ ነው ብለዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ ስለ ነዋሪዎቹ እሮሮ ምላሽ እና የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ቀጣይ ውጥን ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ለከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ ጥያቄውን ብያቀርብም ለዛሬ አልሰመረም፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግር ለመቅረፍ ግን የአዳዲስ አውቶብሶች ግዢን ጨምሮ የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደርግ በተደጋጋሚ ሲያነሳ ይደመጣል፡፡

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ሥዩም ጌቱ
ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ