የማክሰኞ መስከረም 14 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የዓለም ዜና – DW – 14 መስከረም 2017
  1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማክሰኞ መስከረም 14 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የዓለም ዜና

ማክሰኞ፣ መስከረም 14 2017

https://p.dw.com/p/4l2io

አርዕስተ ዜና

*ወደ ሶማሊያ እየገባ ነው በተባለ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ጉዳይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እየተካሰሱ ነው ። የሁለቱም ሃገራት ውጭ ጉዳይ ሚንሥትሮች አንዱ የሌላኛውን ሀገር በህገወጥ የጦር መሣሪያ ማቀበል ጉዳይ ከስሷል ።  

*በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከአንድ ዓመት በላይ ውጊያው በቀጠለበት የአማራ ክልል ባለፈው ዓመት መማር ከነበረባቸው ተማሪዎች ግማሽ ያህሉ አለመማራቸው ተገለጠ ።

*እሥራኤል እና የሊባኖሱ ሒዝቦላህ ዛሬም በሮኬቶች እና በጦር ጄቶች ድብደባ ፈጸሙ ። እሥራኤል በድጋሚ የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩትን ከአየር ላይ በቦንብ ከደበደበች በኋላ እስካሁን የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 560 መድረሱን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል  ።

*የሩስያ ጦር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2022 ጦርነቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በምሥራቅ በኩል እመርታ ዕያሳየ መሆኑም ተዘግቧል ።  ጦሩ ዶንባስ ግዛት ውስጥ እየገሰገሰ ነው ተብሏል ።

ዜናው በዝርዝር

​ሞቃዲሾ፥ ወደ ሶማሊያ እየገባ ነው በተባለ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እየተካሰሱ ነው

ወደ ሶማሊያ እየገባ ነው በተባለ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ጉዳይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እየተካሰሱ ነው ። የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኢትዮጵያ ወደ ሀገራቸው የጦር መሣሪያ በሕገወጥ እያስገባች ነው ሲሉ ዛሬ ወቅሰዋል ። ሚንሥትሩ አሕመድ ሞአሊም ፊቂ ይህን ያሉት፦ የኢትዮጵያ አቻቸው ለሶማሊያ  የሚቀርበው ጦር መሣሪያ በስተመጨረሻ «አሸባሪዎች እጅ ላይ መውደቁ» አይቀርም የሚል ሥጋታቸውን ከገለጡ በኋላ ነው ሲል ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል ። «በውጭ ኃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት መጨረሻው አሸባሪዎች እጅ ላይ ሊወደቅ እንደሚችል»  ሥጋት መኖሩን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተናግረዋል ። ሶማሊያ ለሌላኛዋ ግዛቷ ፑንትላንድ ኢትዮጵያ በሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች የጦር መሣሪያ ድጋፍ ሰጥታለች በሚል ሰሞኑን ክስ አቅርባ ነበር ። ድርጊቱ ሉዓላዊነቷን እንደጣሰ የገለፀችው ሶማሊያ፦ ከዚያም ባሻገር በብሔራዊ ደህንነቷን እና በቀጣናው ሥጋትን የሚደቅን  መሆኑን በመጥቀስ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁኔታውን እንዲያወግዙ አቤት ብላለች ።  አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በበኩላቸው፦ አካባቢውን የግጭት ቀጣና የማድረግ እንቅስቃሴ መኖሩንም ቀደም ሲል ገልጠው  ነበር ።

«ከሶማሊያ ጋር ያለንን አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ፤ በጸረ ሽብር ላይ ያለንን ትብብር አጠንክሮ መቀጠል፤ የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጻረሩ ኃይሎችን የማስተናገድ ብኂሉን፣ አካሄዱን እንዲያቆም ነው የምንጠይቀው ።»

ሶማሊያ ከወራት በፊትም ኢትዮጵያ መሰል የጦር መሣሪያ ዝውውር በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ መፈጸሟን በመጥቀስ ድርጊቱን ኮንና ነበር ። ሶማሊያ ከግብጽ የጦር መሣሪያ ድጋፍ እየወሰደች ያለችው ሠራዊቷን ለማጠናከር ብሎም ከብዙ ሃገራት በተውጣጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል የሚጠበቀው ሰላምና ደህንነቷን ለማሻሻል ለምታደርገው ጥረት አቅም ግንባታ መሆኑን ገልጣለች ። ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ግን ድጋፉ አሳሳቢ ርምጃ መሆኑን በመጥቀስ በብርቱ የተቃወመችው ወዲያው ነበር ። በዜና መጽሄት ተጨማሪ ዘገባ ይኖረናል ።

ደብረማርቆስ፥ አማራ ክልል ከግማሽ በላይ ተማሪዎች አልተማሩም

በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከአንድ ዓመት በላይ ውጊያው በቀጠለበት የአማራ ክልል ባለፈው ዓመት መማር ከነበረባቸው ተማሪዎች ግማሽ ያህሉ አለመማራቸው ተገለጠ ። በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ወደ ትምህርት ቤት መግባት ከነበረባቸው 6 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉ በክልሉ የፀጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት እንዳልተከታተሉ የክልሉ ትምህርት ጽ/ቤት አመልክቷል ። በተለይም በጎጃም ቀጠና የሚገኙ አብዛኛዎቹ የ6ኛ፣ የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና መውሰድ እንዳልቻሉም ተገልጧል ። ችግሩ ሳይቃለል በዚህ ዓመትም ቢሮው 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር ቢያቅድም ከነሐሴ 20 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው ምዝገባ ግን እስካሁን የተመዘገቡት 2 ሚሊዮን እንደማይሞሉ የትምህርት ቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል ።

«ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል አጠቃላይ ወደ 4,8 ሚሊዮን ተማሪዎችን ነበር እንመዘግባለን ብለን ያቀድነው ። 1,3 ሚሊዮን ተማሪዎች ናቸው የተመዘገቡት ። ሁለተኛ ደረጃም 1,2 ሚሊዮን ተማሪዎችን እንመዘግባለን ብለን ወደ ሦስት መቶ ሺህ አካባቢ ተማሪዎች ናቸው የተመዘገቡት ።»

የትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሕፃናቱ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መንግስትና ኃላፊው «በጫካ ያሉ ወንድሞች» ያሏቸው ኃይሎች  ጭምር እንዲተባበሩ ጠይቀዋል ። በመጽሄት ተጨማሪ ዘገባ ይኖረናል ።

ብራንደንቡርግ፥ አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ በበርካታ ወጣቶች መመረጡ አሳስቧል

ጀርመን ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በርካታ ወጣቶች አማራጭ ለጀርመን (AfD) የተባለውን መጤ  ጠል የቀኝ ጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ መምረጣቸው አሳዛኝ ነው ተባለ ። አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ከ11 ዓመታት በፊት ሲመሰረት የያኔዋ መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የፋይናንስ እና የአውሮጳ ፖሊሲን በብርቱ በመቃወም ነበር ። አሁን አንጌላ ሜርክል ከፖለቲካ መድረኩ ገለል ቢሉም መጤ ጠሉ ፓርቲ ግን በከፍተኛ ደረጃ በወጣቶች ዘንድ እየተመረጠ ነው ። በጀርመን የተለያዩ ግዛቶች ዘንድሮ የተካሄዱ ምርጫዎችም ይህንኑ ዐሳይተዋል ። በእሁዱ የቅርብ ጊዜ ምርጫ እንኳን አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ከጀርመን ዋና ከተማ ቤርሊን አቅራቢያ በምትገኘው ብራንደንቡርግ ግዛት በተካሄደ የአካባቢ ምርጫ በሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ «SPD» የተሸነፈው  ከ1 ከመቶ እምብዛም ፈቅ ባላለ የመራጮች ድምፅ ልዩነት ነበር ። በእሁዱ ምርጫ የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ (SPD) ያገኘው 30,9 % ድምፅ ነበር ። በአንጻሩ አማራጭ ለጀርመን  ፓርቲ   በሁለተኛነት ሲያጠናቅቅ 29,2 % ድምፅ መሰብሰብ መቻሉ አነጋግሯል ።  በብራንደንቡርግ የእሁዱ ምርጫ ከየሦስት አንዱ ወጣት ማለት በሚቻል መልኩ አማራጭ ለጀርመን ፓርቲን መምረጡ አሳዛኝም አሳሳቢም ነው ተብሏል ። 

ቤሩት፥ የእሥራኤል ጦር ቤሩት ላይ ሒዝቦላህ በእሥራኤል ግዛት ድብደባ መፈጸማቸው ተዘገበ

እሥራኤል እና የሊባኖሱ ሒዝቦላህ ዛሬም በሮኬቶች እና በጦር ጄቶች ድብደባ ፈጸሙ ። እሥራኤል በድጋሚ የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩትን ከአየር ላይ በቦንብ ከደበደበች በኋላ እስካሁን የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 560 መድረሱን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል  ።  ሮይተርስ በበኩሉ እሥራኤል ዛሬ ቤሩት ላይ ባደረገችው ድብደባ በሒዝቦላህ የሮኬት ክፍል ውስጥ ወሳኝ የተባለ ኃላፊን መግደሏን ዘግቧል ። ሁለቱ ቡድኖች ወደለየት ጦርነት ውስጥ ይገባሉ በሚል ፍራቻም ከደቡብ ሊባኖስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስደት መግባታቸው ተጠቅሷል ። ቤሩት ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው በቤት ውስጥ ሥራ  ተቀጥረው እንደሚሠሩ ይታወቃል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የሊባኖሱ ሒዝቦላህ የእሥራኤል ጦር ሠፈሮች ላይ ፋዲ 3 (FADI 3)በተባሉ አዳዲስ ሮኬቶች ድብደባ መጀመሩን ዛሬ ይፋ አድርጓል ።  ሒዝቦላህ አዲስ የሮኬት ጥቃት መጀመሩን ያሳወቀው በቴሌግራም የመገናኛ አውታር መልእክቱ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል ። ሒዝቦላህ በዩናይትድ ስቴትስ፤ ጀርመን እና በርካታ የሱኒ ዐረብ ሃገራት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ፤ በኢራን የሚደገፍ የሊባኖስ የሺዓ ፖለቲካ ፓርቲ  እና ወታደራዊ ክንፍ ነው ።

ካርኪቭ፥ ሩስያ ከድንበሯ 30 ኪሎ ሜeትር ላይ በምትገኘው የካርኪቭ ከተማ የቦንብ ድብደባ ፈጸመች

ሩስያ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ግዛት በምትገኘው ካርኪቭ ከተማ ውስጥ ባደረሰችው ጥቃት ሦስት ሰዎች ተገደሉ ። በጥቃቱ ቢያንስ 24 ሰዎች መቁሰላቸውም ተገልጧል ።  የሰሜን ምስራቂቱ ከተማ ካርኪቭ ከሩሲያ ድንበር በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች ።  ለሁለት ዓመት ተኩል በፈጀው ጦርነት ከተማዪቱ በሩሲያ የአየር ላይ ጥቃት በተደጋጋሚ ስትደበደብ ቆይታለች ። ለዓለም አቀፍ የማግባባት ሥራ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ሩስያ ሀገራቸው ላይ እያደረሰች ነው ያሉትን ጥቃት እንዲመለከት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጠይቀዋል ።   በካርኪቭ ጥቃት «የሩስያ በቦንብ ጥቃት ዒላማ ያደረገው የመኖሪያ ሕንፃ፤ ዳቦ ቤት፤ ስታዲየም ላይ ነው» ሲሉም ቮሎዶሚር ዘሌንስኪ በማኅበራዊ መገናኛ አውታረ ገጻቸው  ላይ በለጠፉት ጽሑፍ  ገልጠዋል ።  መስኮቶቹ በፍንዳታ  የተበታተኑ እና ፍርስራሹ በመንገዱ ላይ የተከመረ በከፊል የተደረመሰ ባለ ዘጠኝ ፎቅ አፓርትመንትን የሚያሳይ ምስልም አያይዘዋል ።

ሞስኮ፥የሩስያ ጦር በምሥራቅ ዩክሬን በኩል ዶንባስ ግዛት ውስጥ እየገሰገሰ ነው

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዘሌንስኪ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የሩስያ ጦር ብርቱ በሚባል መልኩ በምሥራቅ በኩል ዘመቻ መክፈቱ ተገልጧል ። ጦሩ ሙሉ ወረራ በጀመረበት ወቅት በተደጋጋሚ ለመያዝ ጥረት ወዳደረገበት የዶንባስ ግዛት ደቡባዊ አቅጣጫ በምትገኘው ቩህሌዳር መቃረቡም ተዘግቧል ። ዶንባስ ግዛት ውስጥ የሚገኙት ሴሊዶቭ፣ ቶሬጽክ እና ቩህሌዳር ከተሞች በሩስያ ጦር ስር ሊወድቁ እንደሚችሉ የጦር ተንታኞች ተናግረዋል ። ዩክሬን ከሩስያ ጋር የምታደርገው ጦርነት ፍጻሜው መቃረቡንም ቮሎዶሚር ዜለንስኪ ተናግረዋል። ፕሬዚደንቱ የ«ድል» ያሉትን ዕቅዳቸውን በዚህ ሳምንት ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ለማቅረብ ማቀዳቸውን ይፋ አድርገዋል ። ጦርነቱ የሚጠናቀቀውም ከሩስያ ጋ በመደራደር ሳይሆን፤ «የዲፕሎማሲ ድልድይ በመገንባት» መሆኑን ተናግረዋል ። ምን መሆኑን ግን በዝርዝር አላብራሩም ። የሩስያ ክሬምሊን ቤተመንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔሽኮቭ በበኩላቸው የዩክሬን ዕቅድን በተመለከተ መገናኛ አውታሮች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።  ሩስያ ጦርነቱን ካቆመች የምታቆመውም የምትፈልገውን ግቧን ከመታች በኋላ ነው ብለዋል ። የሩስያ ጦር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2022 ጦርነቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በምሥራቅ በኩል እመርታ ዕያሳየ መሆኑም ተዘግቧል።   

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።