የቀጠለዉ የትግራይ ፖለቲከኞች ዉዝግብ – DW – 13 መስከረም 2017
  1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለዉ የትግራይ ፖለቲከኞች ዉዝግብ

ሰኞ፣ መስከረም 13 2017

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል፣ ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤን፥ ስልጣን ለመጠቅለል በማቀድ፣ የቆየ ቂም በመወጣት እና ሌሎች ከዚህ በፊት በይፋ ያልተሰሙ መረጃዎች በመግለፅ ሲተቹ ተደምጠዋል። ዶክተር ደብረፅዮን እርሳቸው የሚመሩት ህወሓት፣ ሰላም የማይፈልግ አድርጎ የማቅረብ የተሳሳተ ፍረጃ ከትግራይ ባለስልጣናት በኩል እየቀረበበት መሆኑን ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/4kzM0
Äthiopien | TPLF-Treffen im Hauptquartier in Mekelle
ምስል Million Hailesilassie/DW

የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ጀነራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤን ተቹ

በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት መቐለን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ህዝባዊ የተባሉ ስብሰባዎች አካሂዷል። በእነዚህ መድረኮች የፖርቲው አመራሮች ክፍፍል በስፋት መነሳቱ የተገለፀ ሲሆን፥ ህወሓትን ለማጥፋት፣ ስልጣን ለመጠቅለል የሚንቀሳቀሱ ተብለው የተገለፁ አመራሮች በስም እየተጠቀሱ ወቀሳ እንደተሰነዘረባቸው ተሰምቷል።

የትግራይ ገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞች ዉዝግብ እንደቀጠለ ነዉ

ከትላንት በስትያ ቅዳሜ በመቐለ በተካሄደ እና የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮንን ጨምሮ ሌሎች የፖርቲው አመራሮች እና የተመረጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የታደሙበት መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤን፥ ስልጣን ለመጠቅለል በማቀድ፣ የቆየ ቂም በመወጣት እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በማንሳት እንዲሁም ከዚህ በፊት በይፋ ያልተሰሙ መረጃዎች በመግለፅ ሲተቹ ተደምጠዋል። ዶክተር ደብረፅዮን በንግግራቸው እርሳቸው የሚመሩትን ህወሓት ሰላም የማይፈልግ አድርጎ የማቅረብ የተሳሳተ ፍረጃ ከትግራይ ባለስልጣናት በኩል እየቀረበበት መሆኑ የገለፁ ሲሆን፥ ይህ ውሸት ነው በማለት ሲያጣጥሉት ተደምጠዋል።ህወሓት የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን ወነጀለ

ደብረፅዮን "ለምሳሌ በደቡባዊ ዞን በተደረገ መድረክ ጀነራል ፃድቃን እኛ ሰላም እንፈልጋለን፣ እነሱ የሚሹት ጦርነት ነው ሲል ሰምታችሁታል። በጦርነቱ ወቅት ደሴ ተሻግረን ሰሜን ሸዋ ስንጠጋ፥ ድርድር ያስፈልጋል ወይ ሲባል እኔ አዎን ያስፈልጋል ነው ያልኩት። በሰላም ሊፈታ ስለሚገባው። እሱ ግን ከማን ጋር ነው የምንደራደረው፣ ውጊያው አልቋል ሲል የነበረ ነው። አሁን ግን እኔ ሰላም ነኝ እነሱ ጦርነት ናቸው የሚፈልጉ ማለት ጀመረ" ብለዋል።

ጀነራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት
ጀነራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ምስል Privat

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ ካደረገው መደበኛ ስብሰባ በኃላ ትላንት ባሰራጨው መግለጫ፥ በክልሉ ያለው ፖለቲካዊ ችግር በህወሓት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መካከል የተፈጠረ አለመግባባት አድርጎ ማቅረቅ የተሳሳተ ነው ብሏል። ችግሩ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረ ነው ያለው ጊዚያዊ አስተዳደሩ፥ ግዚያዊ አስተዳደሩ የዚህ ውዝግብ አካል እንዳልሆነ ህዝባችን ይገንዘብልን ብሏል። ይሁንና ይህ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል የአስተዳደር ስራዎችን እያደናቀፈ ስለመሆኑ አልካደም። ይህን በትግራይ ኮምኒኬሽን ቢሮ በኩል የተሰራጨ መግለጫ የትግራይ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ስም ማጠልሸት እና ውንጀላ በሕግ ስርዓት እናስይዘዋለን ያለ ሲሆን እነዚህ የፀጥታ ኃይሎች በአስተዳደሩ ስር ሆነው እየተመሩ እና ከፖለቲካዊ አጀንዳዎች ገለልተኛ ሆነው ተልእኮአቸውን እንደሚፈፅሙ ጠቅሷል።

የህወሓት ጉባኤ ዳግም ጦር ያማዝዝ ይሁን?

 የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ እና  የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል
የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ እና የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልምስል Million Haileslasse/DW

በሌላ በኩል የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ቅዳሜ የታሰበውን የዓለም ሰላም ቀን አስመልክቶ በተዘጋጀ መድረክ፥ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ለትግራይ የሰላም ዕድል የፈጠረ ነው ያሉ ሲሆን ከውሉ በኃላ የሚጠበቅ የጦርነቱ መነሻ የሆነ ፖለቲካዊ ምክንያቶችን ለመፍታት የተደረገ ነገር እንደሌለ አንስተዋል።

ጀነራል ታደሰ ወረደ "የፕሪቶርያ ውል ወደ ሰላም አሸጋግሮናል። ወደ ሰላም ተሸጋገርን ማለት ለጦርነቱ ምክንያት የሆነ ነገር በሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መንገድ ልትፈታው ግዴታ መግባት ማለት ነው። በትግራይ ስናይ ሰላም እጃችን ላይ አለች፤ ጦርነት የሆነ ፖለቲካዊ መነሻ ያለው እንጂ ዝምብሎ የሚከፈት ስላልሆነ፥ ለጦርነቱ መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ገና ትግል የሚያስፈልጋቸው ናቸው" ብለዋል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ